Opinion & Analysis

ዶ/ር አብይን በአደባባይ ትእይንተ ህዝብ የመደገፍ ዋንኛ ፋይዳዎች | ከይታገሱ ዘውዱ

የፊታችን ቅዳሜ 16 ቀን በ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ደማቅ የድጋፍ ትዕይንተ ሕዝብ ይደረጋል ተብሎ ከወዲሁ ይጠበቃል። የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ እንደገለፀው የሰልፉ መሪ ሐሳብ “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ” የሚል ነው! የሚል መልእክትአስተላልፏል። መልካምና ሁሉንም አቃፊ የሆነ መሪ ቃል ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ እንደምረዳውየዚህን ሰልፍ ዋንኛ ፋይዳ የሚከተሉት አብይ ጉዳዮች ይመስሉኛል: –

የተጀመረው የለውጥ ሂደት ከፍተኛ መሰዋዕትነት ተከፍሎበት የመጣ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለውጡን እና ወጤቱን ለመቀበል የሚጎፈንናቸው አፅራሪ ለውጥ የሆኑ ወገኖች አሉ። እነኚህ ወገኖች በተለያየ የዳቦ ስም ይጠራሉ። ለምሳሌ ጡረተኞች (oldgards) (መቼም ጊዜ ደግ ነው እነሱም ተራቸው ደርሶ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች ሊባሉ በቅተዋል)፣ በሰሞንኛው ስያሚያቸው ደግሞ የቀን ጅቦች የተባሉት ናቸው። እነማናቸው ከተባለም በዋንኛነት የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ሲሆኑ፣ የታሰሩበት የባርነት ገመድ እንደተፈታ አወቀው እንዳላወቁ የሆኑ አገልጋዮች ከተለያዩ ዘውግ የሚመዘዙ የገዢው ፓርቲ ብብት ውስጥ ሆነው የሚያገላጅጁትን ይጨምራል። ነገር ግን ይህ ፍረጃ በፍጽሞ የትግራይ ህዝብን በጅምላ የሚመለከት አይደለም።
እነኝህ አፅራሪ ለውጥ የሆኑ ወገኖች አእምሮቸው ዝጓል። ለውጡን እና ውጤቱን የመቀበል ፈቃዱም ሆነ ዝግጁነቱ የላቸውም። በዘረፋ፣ በግድያ፣ በጭቆና፣ በዘረኝነት እና በሰው ልጆች ስቃይ መከራ የገነቡት ውስጣዊና ውጪያዊ አለምቸው (empire states) አላቸው። ውስጣዊው አለምቸው በዎች ሰቆቃና ስቃይ የሚነቃቃ የተመመ መንፈሳቸው (emotional pain body) ሲሆን በሰው ልጆች ደም ካልታጠበ እረፍት ይነሳቸዋል። ስለሆነም ለስሜት ህመማቸው መኖ ይሆን ዘንድ ለ27 አመታት በዘሩት የዘረኝነትና የጥላቻ መርዝ ተጠቅመው ህዝብን በህዝብ ላይ እያነሳሱ ከማባላት የማይመለሱ ለመሆኑ ከሰሞኑ ደቡብ ኢትዮጵያ ያየነው አሰቃቂ የዘር ጠረጋና ግድያ (ethnic cleansing and genocide) መሰል ሙከራዎች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው። ውጫዊ አለማቸውም እንዲነካ አይፈቅዱም። የህዝብንና የሃገርን ሃብት ከመዝረፍና ከመቦጥቦጥ አልፈው ተርፈው ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ሳይቀር ሃገሪቱን አሲዘው ተበደረው፣ የተበደሩት ገንዘብ ሃገር ቤት ሳይደርስ ግማሹን ከሃገር ውጪ ጠልፈው ያስቀሩ፣ ሃገር ቤት የመጣውን ተቀራምተው የራሳቸውን ኑሮ ያደላደሉ በመሆናቸው፣ የዘረጉት የዘረፋ መረብ፣ ያከማቹት ሃብትና ንብረት እንዲነካ አይሹም እና ለውጡን ፈፅሞ ይቃወማሉ። በተቻለ መጠን ሁሉ ለውጡን ሊቀለብሱ ይሞክራሉ። ለዉጡ ሲገፋ የዘረፉት መሬት፣ ያከማቹት ገንዘብ፣ የገነቡት ፎቅ ለጥያቄ ይቀርባል። በመሆኑም በሚቆጣጠሩት የፀጥታ ሃይልና የኢኮኖሚ አቅም እያስፈራሩ ለውጡ እውን እንዳይሆን መከላከላቸው የሚጠበቅ ሃቅ ነው።

በመሆኑም የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ ዶ/ር አብይና የሚመሩት ለውጥ አራማጅ ቡድን ለፈጠረው የለውጥ ተስፋ እውቅና ከመስጠት፣ ምስጋና ከማቅረብ አልፎ ህዝብ ሰላማዊ የለውጥ ሂደቱ አደጋ ሳያጋጥመው ወደ ፊት እንዲራመድ ለሚደረገው ጥረት ሰፊ ድጋፍ እንደሚሰጠው በአንድ ቃልና መንፈስ የሚናገርበት አጋጣሚ ነው። ሰልፉ ዶ/ር አብይን ከማወደስ ይሻገራል ሲባል፣ ለውጡን ወደ ኋላ ለመጎተት ለሚሹ ወገኖች ህዝብ ጠንካራ አቅምና ጉልበት እንዳለው በማሳየት አፅራሪ ወገኖችን ማስታገስ ነው። ለውጡ አይቀለበስም የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ የሚያስፈልገውም በህዝብ ስም በህዝብ መካከል ለሚሽሎከለኩ እስስታዊ ባህሪ ላላቸው ጓዶች በቃችሁ ወደ ኋላ አንቀለበስም የሚል የጨዋ መልክት ማስተላለፍን የሚጨምር ነው ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላለው ጉዳይ የድጋፍ ሰልፉ ተምሳሌታዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ ነው። ዘመን እና ሁኔታን ተሻጋሪ ተምሳሌት ይሆናል። መሪዎች በጎ ነገሮችን ለህዝባቸው ሲሰሩ ህዝብ ቀስቃሽና አስታዋሽ ሳያሻው በፍቃዱ አደባባይ ወጥቶ የሚያወድስ ለመሆኑ፣ በዛው መጠን ሲሳሳቱና አቅጣጫቸውን ሲስቱም የሚያርቃቸው እንዲያም ሲል የሰጣቸውን ክብር ነፍጎ የሚያሰናብታቸው ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ይሆናል። በመሆኑም የድጋፍ ሰልፉ በጊዜ ሂደት ወደ ተቃዋሞ እንዳይለወጥ ለነ ዶ/ር አብይ ጠንካራ መልክት ከማስተላለፍ አልፎ ትጉሃን እንዲሆኑ የበለጠ ያናቃቸዋል። ያከበሩት ህዝብ እንዳከበራቸው ሁሉ የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን እንዲሆን ካገዙት ሁሌም ከጎናቸው ሆኖ ለግባቸው መሳካት ያግዛቸዋል።

ዴሞክራሲን ማጽናት ሁለተኛው ፋይዳ ነው። ከአንባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረግ ሽግግር ባጭር ጊዜ ውስጥ ህግና ፖሊሲ በመቀየር ብቻ እውን የሚሆን ጉዳይ ሳይሆን ልምምድን የሚጠይቅ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት መመሥረት አለባቸው። በመቀጠል የሃገራችንን ፖለቲካዊ ባህል መቀየር ያስፈልጋል። እነኚህ ልምምዶች በተለያየ ደረጃና መጠን የሚገለጡ ቢሆምን አንደኛው ማሳያ ይህን መሰሉ ዴሞክራሲን የሚያወድስ ትይንተ ህዝብ ማካሄድን ይጨምራል። እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ይሆን ዘንድ የህዝብ ግፊት (popular pressure) ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ህዝብ የሰጡትን ብቻ አሜን ብሎ የሚቀበል ሳይሆን የጎደለውን የሚጠይቅ፣ የተሰራውን ደግሞ የሚያወድስ ሲሆን ነው ይመጣል የተባለው ዴሞክራሲ የጸና መሰረት እንዲኖረው እድል የሚፈጠረው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግርና ማጽናት (democratic transtion and consoludation) ህዝብን ያሳተፈ ሲሆን ገዢዎች የሚጭኑት ስረዓት መሆኑ ይቀርና ዜጎች አሻራቸውን ያሳረፉበት፣ የኔ የሚሉት የላባቸውና የደማቸው ፍሬ ይሆናል። ዶ/ር አብይና ቡድናቸው የለውጥ ፋና ወጊ ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲና የነጻነት አባት ሆነው ስማቸው በወርቅ ቀለም ደምቆ ይጻፍ ዘንድ የህዝቡን የዴሞክራሲ ጥማት፣ የለውጥ መሻት በሚገባ የሚረዱበት አጋጣሚ የሚሆነው በመንግስት አነሳሽነት በተጠራ ሰልፍና ስብሰባ ሳይሆን ይህን መሰሉ የዜጎች ነፃ ፍቃድና ፍቅር የቀሰቀሰው ንቅናቄ ውስጥ ነው። ይህ አይነቱ ትእይንት ለለውጥ አራማጅ መሪዎቹ ማጣቀሻ ብቻ ሳይሆን የሚሆናቸው ጉልበታቸው ሲዝል ብርታት ጭምር በመሆን የጀመሩትን ለውጥ ከጫፍ እንዲያደርሱ የወኔ ስንቅ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያዊነትንማንገስየዚህትዕይንተህዝብዋናውናመሰረታዊውተልዕኮይሆናልብየአስባለሁ። ለሦስትአስርትአመታትሲንቋሸሽእናሲጥላላየነበረውኢትዮጵያዊማንነትቀንወጥቶለትወደቀድሞስፍራውበክብርተመልሷል። ዜጎችቋንቋናሃይማኖት፣ ዘውግናርዕዮትአለምሳይለያቸውለአንድሃገራቸውበጋራየሚዘምሩበት፣ የሚቀኙበትናፍቅራቸውንየሚገልፁበትከበርካታአመታትበኋላየመጣብቸኛአጋጣሚነው። የመጀመሪያውእንጂየመጨረሻውአይሆንምብየምአስባለሁ። እድሜለለውጥሃይሎች፣ እድሜለጽኑታጋይየኢትዮጵያልጆች፣ እድሜለቄሮናፋኖ፣የመታገልግባቸው፣ የሞትግርፋታቸው፣የስርስደታቸውፍሬለሆኑትበተለይም እድሜ ለነ ዶ/ር አብይ፣ አቶ ለማ፣ አቶ ደጉና አቶ ደመቀ እና ሌሎችም በስርአቱ ውስጥ የበቀሉ የአዲሱ ትውልድ ቆራጥ የለውጥ መሪዎች ይሁና እነሆ ታሪክ ተቀይሯል። ዛሬ ኢትዮጵያ ስንል ደስ እያለን በኩራት ነው የሃገራችንን ስሟን የምናነሳው። ትላንት በስሜት ሆኖ ኢትዮጵያ ትበተን የሚለው ወገኔ ዛሬ ወደ ቀልቡ ተመልሶ ኢትዮጵያን እናድን ወደሚል መደመር ውስጥ ገብቷል። ይሄ የሆነው አርቆ አሳቢ፣ ዘመን ተሻጋሪ መልክት ያለው፣ እውነት የሚናገር፣ ለጠፋው ጥፋት የሚጸጸት፣ ይቅርታ የሚጠይቅ፣ በግፍና በግብዝነት ጨለማ ቤት ውስጥ የወደቁትን ጉፉአንን አርነት የሚያወጣ፣ ትላንት ላይ ተቸክሎ የሚያንጎላጅጅ ሳይሆን ነገን ብሩህ ለማድረግ የሚተጋ፣ እርቅን፣ ሰላምን፣ ይቅርታን እና መቻቻልን የሚሰብክ መንገድ ጠራጊ፣ ሰው የሆነ የሰው መሪ ሃገራችን ዛሬ በመታደሏ ነው። ጸጋችን የተገፈፈው፣ መከራችን የበዛው፣ ግፋችን የተቆለለው ሰውነታቸውን ዘንግተው መንፈሳዊ መክሊታቸውን ሸጠው፣ በቁሰ-አካላዊ ጎስቋላ ፍልስፍና እራሳቸውን ቁስ-አካል አሳክለው ለሺህ አመታት ይኖሩ የመስላቸው የነበሩ ሃሳበ ድኩማን፣ ሲመሩን ሳይሆን የትኛውንም ዋጋ አስከፍለውን ሲገዙን የኖሩ፣ ከላያችን በተጫኑ ኮተታም ገዢዎች የተነሳ ነው። ሞቱ፣ ስደቱ፣ ዋይታና መከራው ብርትቶ ዛሬ ሰው በሰው ላይ ጨክኖ በዘረኝነት እርኩስ መንፈስ እንዲነሳሳ ያደረገው ከሰውነታቸው ተጣልተው፣ ከኢትዮጵያዊ ባህላቸው እና እምነታቸው ተፋተው ለሃገራዊ ቱውፊታቸው ዋጋ ነስተው፣ ከሰው መንደር በቀላወጡት የተሳከረ አስተምሮ ተሳክረው እንግዛችሁ ባሉ ነው ይሄው ዛሬ ወደ ገባንበት ቅርቃር ያደረሱን።
እንደመር፣ በፍቅር ተያይዘን ዘመን እንሻገር፣ መጠላላቱ፣ መባላቱ፣ በጨራረሱ አይጠቅመንም የሚል መሪ ሲገኝ አብዛኛው የሃገሬ ሰው በደስታ ተቀብሎታል። ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ሲል አቶ ለማ የስንቶቻችን አንጀት ተላወሰ? እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን ሲል ዶ/ር አብይ የስንቶቻችን አይን እንባ አቀረዘዘ? ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው። የአንድ ጎሳ፣ የአንድ ዘውግ፣ የአንድ ሃይማኖት አልያም የአንድ ርዕዮተ አለም ተከታዮች ሳትሆን ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ቤት፣ የሁሉም ዜጋ ዋስትና እና ክብር ነች። የኢትዮጵያ ዳግም መነሳት መሲህ የመጣው ኩርማናዊ ዘውገኞች እንዳሰቡት ከአቢሲኒያ አይደለም። ይልቁንም እነሱ ህዝብን ለመነጠል ከሚጠቀሙበት የኩሽ ምድር ነው የበቀለው። ዛሬ ያ ሁሉ መፈራረጅ ቀርቷል። ዘመኑ ዶ/ርአብይ እንደሚለው የመደመር ብቻ ነው። የጸብ፣ የጥላቻ፣ የክርክር፡ የምረዛ፣ የማግለልና መገለል ምዕራፉ መዘጋት አለበት። ኢትዮጵያ አስኳል ሆና የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን ማስተሳሰር የሚቻልበት ዘመን እሩቅ አይሆንም። ፍቅር ሃገራችንን አንድ ያደርጋታል። ይህ እውነታ በምእላትና በስፋት ከሚገለጥባቸው ቀኖች አንዱ ደግሞ ሁሉንም ወገን የሚጋብዘው ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሰው የቅዳሜው የአደባባይ ትእይንተ ህዝብ አንዱ ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊነትን በሚያወድስ ተእይንተ ህዝብ ላይ የሚወገዝ ካለ አንድ አካል ብቻ ነው እሱም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላት የሆነው ገዢ መደብ ብቻ (ህወሓትና አጫፋሪዎቹ)። ገዢ መደብን ማውገዝ ማለት ደግሞ ዘውግን ወይን በአዘቦታዊው ቋንቋ ብሔርን ማውገዝ ማለት አይደለም። በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣ የለውጡ ደጋፊና ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ አሞጋሽ የሆኑ ሁሉ ቋንቋና ዘውግ፣ ሃይማኖትና ባህል ሳይለያቸው አደባባይ ተገኝተው ለኢትዮጵያዊነት ይዘምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዋናው ጉዳይ የድጋፍ ሰልፉ የተሳካና የታለመለትን ግብ የሚመታ እንዲሆን ዜጎች ከፍተኛ ሃላፊነት መውሰድ ይገባቸዋል። ሰልፉ ከታለመለት አላማ ውጪ ወጥቶ የጥላቻና የጥፋት መልዕክት የሚተላለፍበት እንዳይሆን ሁሉም የበኩሉን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል። የጥፋት ሃይሎች በመንጋው መካከል የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች አስገብተው ትንኮሳ ሊያካሂዱም ሆነ ሰዎችን ለቁጣ የሚያነሳሳ ነገር አያደርጉም ተብሎ አይጠበቅም። በየተኛውም መንገድ የሚመጣን የጥላቻና የጥፋት አካሄድን መከላከልና በትግስት ማለፍ ዶ/ር አይን እና ኢትዮጵያን እወዳለሁ፣ ለውጥና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እደግፋለሁ ከሚል ወገን ሁሉ የሚጠበቅ ግዳጅ ነው። ከ13 ዓመታት በፊት ሚያዚያ 30 ቀን ቅንጅት በጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የታየው ጨዋነትና ኢትዮጵያዊነት በዚህኛው ሰልፍ በስፋት ይጠበቃል ብለን እናምናለን።

የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቀን!

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top