Opinion & Analysis

ተቃውሞ ድሮና ዘንድሮ:- በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድን መቃወም ይከብዳል፤ አላስፈላጊ ዋጋም ያስከፍላል | ዶ/ር አሸናፊ ጐሳዬ

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል ሁሉ እንደሚረዳው ውጤቱን አስቀድሞ በእርግጠኝነት መተንበይ ባይቻልም ሀገራችን በለውጥ ሂደት ውስጥ በማለፍ ላይ ነች።

በኢህአዴግ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረውና ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን፣ መከላከያ እና ደህንነቱን በፍጹም የበላይነት ሲቆጣጠር የቆየው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከባድ ፈተና እንደገጠመው ግልፅ ነው። የነጻነት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የዕኩል ተጠቃሚነት እጦት የወለደውና ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሕወሓትን ብርክ ሲያሲዘው በሌላ በኩል ደግሞ በጠባብነትና በትምክህተኝነት እየፈረጀ ሲያሸማቅቃቸው የነበሩት የግንባሩ አባል ድርጅቶች መሪዎች የተተበተቡበትን የፍርሃት ሰንሰለት በጣጥሰው በመጣል፣ ከሕዝብ ጋር በመቆምና የለውጡ አካል በመሆን ሕወሓትን እርቃኑን አስቀርተውታል። እንደሰማነው ከሆነ በቅርቡ የግንባሩን መሪና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በመምረጥ ሂደት ውስጥ በእነ አቶ ለማ መገርሳ የተመራው ኃይል ሕወሓትን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ስልጣን የተረከበበት ስልትና ሂደት የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ተስፋ ሰጪም ነው።

በዚያው አንፃር ሀገራችን አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። በአንድ በኩል “ሕወሓት አሸለበ እንጂ ገና አልተኛም፤ የነበረውን ለማስቀጠል የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም” ብለው የተሰለፉ ኃይሎች የመኖራቸውን ያህል የመገንጠል አጀንዳ ያላቸው ጠባብ ብሄርተኞችም ህልማቸውን ለማሳካት አጋጣሚው እስኪፈጠርላቸው ማድፈጥን መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የሚመራው እንቅስቃሴ ጥገናዊ እንጂ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ ስለማያመጣ ያ እስኪሆን ትግሉ መቀጠል አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።

ለዚህም ነው ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ የሚበጀው መንገድ የቱ ነው የሚለው ጥያቄ በስፋት መነጋገርያ የሆነው። በተለይም የተገኙትን ድሎች አስከብሮ ለበለጠ ድል ቀጣይነት ያለው ትግል ማድረግ ወይስ የሚከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ ተከፍሎ ለስርነቀል የስርዓት ለውጥ ትግል መቀጠል ይሻላል በሚለው ጥያቄ ላይ የሀሳብ ፍጭት የተጧጧፈው።

እንዲህ ዓይነቱ የሀሳብ ፍጭት ብዥታን አጥርቶ እና፣ ልዩነትን አጥብቦና ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ከመርዳቱም በላይ የጋራ ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖረንና ለተግባራዊነቱም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ላይ እንድንጓዝ መንገድ ይጠርጋል፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አጠቃላይ ራዕያቸው፣ ሀገሪቱን እንዴት እንደሚመሩና ሊተገብሯቸው ስላቀዷቸው የሩቅና የቅርብ ጊዜ ግቦች ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ያደረጓቸውን ንግግሮች መፈተሽ፣ መቃወም ወይም መተቸትን ጨምሮ።

ቀጥሎ የዶ/ር አብይን ንግግሮች እና አቋሞች:- 1) ከብሄራዊ መግባባትና እርቅ ከማድረግ፣ 2) የሀገር አንድነትን ጠብቆ ከማቆየት፣ 3) የዲሞክራሲ ሥርዓትን ከመገንባት፣ 4) የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን እውን ከማድረግ 5) መልካም አስተዳደርን ከማስፈን፣እንደዚሁም 6) ከለውጥ አራማጅነት አንጻር በማየት ለምን በቅርቡ የተቃውሞ አጀንዳዎቻችን መቀየር እንዳለባቸውና እሳቸውን በነዚህ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መቃወም እንደሚከብድ ለማሳየት እሞክራለሁ።

1) ከብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ አንጻር

“መጪው ጊዜ በኢትዮጵያ የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው” ብሎ ለሰላም እጁን የዘረጋን መሪ መቃወም ለእርቅና ሰላም መልእክተኞች ይከብዳል።
በሰላማዊ መንገድ የመንግስት ስልጣን ሽግግር ማድረግ ሳንችል ቀርተን በቂምበቀል እና አሮጌውን በኃይል አስወግዶ በአዲስ መተካት ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ባህላችን ዘርፈ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ለዘመናት ዘልቋል። መቻቻል ጠፍቶ በየጊዜው የእርስበርስ ግጭቶች በየቦታው እየተከሰቱ ዜጎች በግፍ እየተገደሉ፣ ነፍሳቸዉን ለማዳን ከኖሩበት አካባቢ እንዲሸሹና በግድ እየተፈናቀሉ ዘላቂ ሰላምን አጥተው ኑሯቸውን እንዲገፉ ሆነዋል። በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን፣ ተደራድረንና ተግባብተን በጋራ ጉዳያችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ ባለመቻላችን የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ኖሮን ለዘላቂ ሰላምና እድገት መረባረብ አልቻልንም።

እነዚህንና ሌሎች ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፉ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ ነው እያሉ ብዙ የፖለቲካ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ቢመክሩም ሰሚ አጥተው “ማን ከማን ተጣላና ነው እርቅ የሚያስፈልገው” ተብሎ እየተላገጠባቸው በዚህ ረገድ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች ሳይሰሩ ቀርተው የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ይህ ለዘላቂ ሰላማችንና ለቀጣዩ አብሮነታችን ወሳኝ ነው ይላሉ።
“በሀገር ውስጥም ሆነ በስደት ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምዕራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምዕራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡”
በእኔ እምነት ይህ ጥሪ ለይስሙላ የተባለ ሳይሆን ከልብ የመነጨ ነው። እነሆ ተግባራዊነቱም ታዋቂውን የነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ብዙ የህሊና እስረኞችን በመፍታት ተጀምሯል። ተመሳሳይ እርምጃዎች በቀጣይነት እንደሚወሰዱም ተስፋ አለኝ። ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ ደግሞ እውን የሚሆነው ሁሉም ወገን ይቅር ለመባባል ወደ ሰላም ጠረጴዛው በሙሉ ፈቃደኝነትና ቅንንነት ሲመጣ እንጂ ከአንድ ወገን እንዲቸር በመጠበቅ አይደለም። ፍትህና ማህበራዊ መረጋጋት የሰፈነበት የፖለቲካ ስርዓት በአገራችን እንዲሰፍን በጭፍን ጥላቻና በክፋት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ቅኝታችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለውጠን ስለእውነተኛ ፍቅር፣ ከልብ የመነጨ ይቅርታ፣ ዘላቂ ሰላም፣ ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ ስለመኖር እያቀነቀንን ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ከመተባበር የተሻለ አማራጭ ያለን አይመስለኝም።

2) የሀገር አንድነትን ጠብቆ ከማቆየት አንጻር

“ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል” ብሎ የተነሳን መሪ መቃወም ለአንድነት ኃይሎች እጅግ ይከብዳል ወያኔ በዋነኛነት ከሚነቀፍባቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ መጣሉ ሲሆን ይህን ለመቀየር ይህን ሁሉ ዘመን ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀርበዋል። ለምሳሌ አምና ግንቦት 19 እና 20 ሲያትል ከተማ ውስጥ በተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ ሲጠናቀቅ የወጣው የአቋም መግለጫ ተጠቃሽ ነው።

“ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክና የስብጥረ-ሕዝብ ባለፀጋ ነች፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የማንነታችን መግለጫ የሆኑት ብሄር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይለያዩን ተጋብተን፣ ተዋልደን፣ ተከባብረን እና በፍቅር በደግም ሆነ በክፉ ግዜ ሀገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን ኖረናል፡፡ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብን ከህዝብ ለመነጠል፤ ተዋልደውና ተባብረው ለዘመናት የኖሩትን የሀገሪቱ ህዝቦች ለማቃቃር የሚሰሩ ኃይሎች ተደጋግመው እያታዩ ነው። ከነዚህ ኃይሎች ደግሞ ዋነኛው ሀገሪቱን በብሔርና በሀይማኖት በመከፋፈልና እርስ በርስ በማጋጨት የስልጣን ዕድሜውን እያራዘመ ያለው ወያኔ/ኢህአዴግ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን ተምረን፤ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ላይ አተኩረን ይህን የተጋረጠብንን ብሄራዊ የመበታተን አደጋ ለመቀልበስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንነሳ አበክረን እንጠይቃለን፡፡”

ለዚህ ሕዝባዊ ጥሪ መልስ ለመስጠት አስበው ይመስላል ዶ/ር አብይ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት ደብዝዞና አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው ብሄራዊ አንድነታችን መልሶ ጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ሁላችንም ተባብረን እንድንሰራ በመጀመሪያው ንግግራቸው ጥሪ ያቀረቡት።

“ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች፣ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል፡፡……. ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ እንደ ተለያየ ሀገር ዜጋ በባዕድነትና ባይተዋርነት ሳይሆን፣ ሁላችንም እንደ ባለቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ሲሆን ስንወድቅም፣ ስንነሳም በጋራ ይሆናል፡፡”

ታዲያ ዶ/ር አብይ ይህን በማለታቸው በአንድ በኩል የነበረው ከፋፍለህ ግዛ ስርዓት እንዲቀጥል በሚፈልጉ ኃይሎች በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነትን በማይቀበሉ ጠባብ ብሄርተኞች ተቃውሞ ሲገጥማቸው የአንድነት ኃይሉ ከእሳቸው ጎን ቆሞ የሀገሩን አንድነት መጠበቁን ከማረጋገጥ ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ አለው? በእኔ እምነት በጭፍን ከመቃወም ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን የሀገር አንድነትን ጠብቆ የማቆየት ቃልኪዳን እንዲያከብሩ በየጊዜው እያሳሰብን ለሁላችንም የምትመች፣ ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣እውነተኛ እኩልነት፣ ፍትህና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር እንድትኖረን ለማድረግ በጋራ ብንረባረብ ይሻላል።

3) የዲሞክራሲ ሥርዓትን ከመገንባት አንጻር

“እኛ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲና ነፃነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም!” ብሎ ጥሪ የሚያቀርብን መሪ መቃወም ለዴሞክራቶች ይከብዳል።

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ወያኔ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አንዴ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአንድ አውራ ፓርቲ የሚመራ ልማታዊ መንግስት ነው እያለ ፖለቲካውን ሙሉበሙሉ በመቆጣጠር ፍጹም አምባገነናዊ ሆኖ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ችሏል። አፋኝ ህጎችን በማውጣትና መዋቅሮችን በመዘርጋት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ከሆኑት ውስጥ የህግ የበላይነት ጠፍቶ አድሎና ኢ-ፍትሃዊነት ሰፍኖ፤ የፕሬስ ነፃነት ተዳፍኖ የመገናኛ ብዙሀን የሕዝቡን ፍላጎት ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ራዕይና ዓላማ የሚያራምዱ ሆነው፤ ልዩነትን ማስተናገድ ሳይቻል ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦችን ሽብር ፈጣሪዎችና ሀገር አፍራሾች አድርጎ መክሰስ ፤ መሠረታዊ የሚባሉ ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ዜጎች በግፍ እንዲገደሉ፣ በየእስርቤቱ እንዲማቅቁና ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ሲደረግ ቆይቷል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህ ማብቃት አለበት ይላሉ።
“ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መደማመጥን ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ ሀገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው፡፡ መንግሥት የሕዝብ ሀገልጋይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገዥ መርሐችን የሕዝብ ሉዓላዊነት ነውና፡፡ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የመጀመርያውም የመጨረሻውም መርሕ፣ በመደማመጥ የሐሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የእኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡”

የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስፈን ለዓለም ሰላም ወሳኝ ነው በሚባልበት በ21ኛው ክፍለዘመን ይህን እውን ማድረግ ለእኛ ኢትዮጵያውያን አይገባችሁም ብሎ የሚከራከር አንድም የዜጎችን መብት ሁሉ ረግጦ የስልጣን ጥሙን ለማርካት የሚተጋ አምባገነን አሊያም አላዋቂ የዋህ ብቻ ነው። ስለሆነም በመሰረተ-ሀሳቡ ላይ ከዶ/ር አብይ ጋር የጎላ ልዩነት የለንምና ከሳቸው ጋር በመተባበር የአፈና ህጎች ሁሉ እንዲወገዱና መዋቅሮቹ እንዲፈርሱ፣ ነፃና ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡና አዲስ የፖለቲካ ባህል በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ሁላችንም ብንረባረብ የተሻለው አማራጭ ነው።

4) የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን እውን ከማድረግ አንጻር

“ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር” አደርጋለሁ ብሎ የተነሳን መሪ መቃወም ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ደጋፊዎች ይከብዳል።

ወያኔ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን አዎንታዊ ሚናን ያለመቀበል ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ምህዳሩን ከጊዜ ወደጊዜ በማጥበብ እነሱን ማዳከም መንግስታዊ ፖሊሲ አድርጎ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባሎችን ማሰርና ማሰቃየት ዋና ተግባሩ ሆኖ ቆይቷል። በእውነተኛ የህዝብ ምርጫ ስልጣኑን ማጋራትም ሆነ መልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ አንዴ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሌላ ጊዜ ወደ አውራ-ፓርቲ ዲሞክራሲ ተሸጋግረናል እያለ በፍፁም አምባገነንነት ዘልቋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ መቀየር እንዳለበት አጠያያቂ አይደለም፤ ወደ ትክክለኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መሸጋገር አለብን፤ ይህን እውን ለማድረግም ሁላችንም በቅንንነት እንድንነሳ ይጠይቃሉ።

“ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎች የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደ መጣ ሀገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግሥት በኩል ፅኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ ስለሰላምና ፍትሕ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡”

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥሪዎች ቢቀርቡም መተማመን ጠፍቶ ምንም ውጤት አላመጡምና ተቃዋሚዎች ይህንንም በጥርጣሬ ቢመለከቱት አይገርምም። ሆኖም ያ ያለመተማመን አዙሪት አንድ ቦታ ላይ መሰበር አለበት። የዶ/ር አብይ ንግግር ሸፍጥ የሞላው ስለማይመስል እድል መስጠቱ አይከፋም። እንደ እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል እውን እንዲያደርጉ፣ ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖርና የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን አቅርበው ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉትን ተወካይ በነጻነት መርጠው

ለስልጣን ማብቃት የሚችሉበትን የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ የሁላችንንም አስተዋፅኦ የሚጠይቅበት ጊዜ ነው። ለዚህም የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉዋቸውን ጥቃቅን ልዩነቶች አቻችለውና “እኔን ያልደገፈ ሁሉ ጠላት ነው” ከሚል ጽንፍ ወጥተው በመተባበርና በመዋሃድ ቁጥራቸውን ከዘጠና ወደ ዘጠኝ ወይም ከዛ በታች የሚወርድበትንም መንገድ ቢያስቡበት ይጠቅማል።

5) መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር

“ዋነኞቹ የሀገራችን ችግሮች ድህነት፣ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር ዕጦት” መሆናቸውን ተቀብሎ እነዚህን ለመለወጥ ቆርጬ ተነስቻለሁ የሚልን መሪ መቃወም ለመልካም አስተዳደር ናፋቂዎች ይከብዳል
መልካም አስተዳደር እድገትንና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ያምናሉ። ከመልካም አስተዳደር ባህርያት መካከል የህግ የበላይነት፣ ፍትሃዊነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ዋነኞቹ ናቸው። የወያኔን አገዛዝ ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት አጥብቀን ስንቃወም የነበርነው በዋናነት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች፣አድሎና የፍትህ መዛባት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዜጎች በገፍ ሥራ ማጣትና መሰደድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ነበር። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተካሄዱ ያሉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች የመልካም አስተዳደር እጦት ውጤቶች መሆናቸውን አዲሱ መሪ ከኛ ጋር ይስማማሉ። ይህንንም ለመለወጥ ቆርጠው መነሳታቸውን ይገልፃሉ።

“የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስናና ብልሹ አሠራር መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ተደማምረው ሰፊና ውስብስብ ፈተና ደቅነውብናል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወገኖቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለመፈናቀል፣ ለሕይወትና ንብረት መጥፋት ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል፡፡”

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል ካለባት እነዚህ ዘርፈ- ብዙና ውስብስብ ችግሮች መውገድ አለባቸው። ችግሮቹን የማስወገድ ኃላፊነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ አይደለም። የዜጎቿን ሁሉ ርብርብ ይፈልጋል፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ አብሮ መጓዝን ይሻል፤ በአንድ ጀንበር የሚከናወን ስላልሆነ ትንሽ ትዕግስት ማድረግን ግድ ይላል። ከዛ ውጪ ጣት መጠቋቆም ወይም መወነጃጀል ስቃያችንን ያረዝመው እንደሁ እንጂ ከገባንበት አረንቋ ሊያወጣን አይችልም።

6) ከለውጥ አራማጅነት አንጻር

“ከብሔረተኛው የህወሓት ከፋፋይ ስርዓት የተለየ ግልጽ አቋም በይፋ በማንጸባረቅ ፋና ወጊ” ያሉትን ኃይል መልሶ መቃወም ለሲያትል ጉባዔ ተሳታፊዎች ይከብዳል።

ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ከየካቲት 9 – 12 ቀን 2010 ዓ.ም (February 16-19, 2018) በሲያትል በተካሔደው ጉባዔ ተሳታፊ የነበሩ ከ26 በላይ በሀገር ውስጥና ውጭ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋና የፖለቲካ ድርጅቶች ዶ/ር አብይንና ጓዶቻቸውን ካደነቁ በኋላ የለውጥ አራማጅነታቸውን ባወጡት መግለጫ ማረጋገጣቸው አይዘነጋም።

“የህዝቡን ስቃይ፣ መከራና መሠረታዊ ፍላጐት በመረዳት በተለይም ሀገሪቷ ያለችበትን የፖለቲካ ቀውስ በማጤን ከሕዝብ ጐን ለመቆም ተነሳሽነት ላሳዩት እና በሀገር አንድነት ዙሪያ ከብሔረተኛው የህወሓት ከፋፋይ ስርዓት የተለየ ግልጽ አቋም በይፋ በማንጸባረቅ ፋና ወጊ ለመሆን ለደፈሩት ለኦህዴድ አመራሮች በተለይም ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለዶ/ር አብይ አሕመድና ለአቶ አዲሱ አረጋ ያለንን አክብሮት እና አድናቆት ሳንገልጽ አናልፍም።”
መግለጫው በተጨማሪም ለብአዴን፣ ኦህዴድና ለደሕዴግ አባላት የሚከተለውን ጥሪ አድርጎ ነበር።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ነፃነት የሁላችንም የትግል ውጤት ነው። ሕዝቦች በእኩልነትና በመከባበር የሚኖሩባት ሀገር እንድትኖረን የምታደርጉትን ጥረት እናከብራለን፣ እናደንቃለንም። ወደፊትም ለሁሉም ዜጎቿ ምቹና ፍትህ የተሞላባት ሀገር እውን ትሆን ዘንድ የሁላችንንም ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ይጠይቃልና የበኩላችሁን የዜግነት ግዳጅ ትወጡ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።”

ታዲያ ከላይ ጥሪ የቀረበላቸውና የቆማችሁለት ዓላማ ህዝባዊ ነው፤ ድላችሁም ድላችን ነውና በርቱ የተባሉት ኃይሎች እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ በመተባበር የወያኔን ሴራ አክሽፈውና ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ድል ሲቀዳጁ እንዴት ብለን ነው ወደ ጠላት ጎራ ፈርጀን እንታገላችሁ የምንለው? በእኔ እምነት እነዚህን የለውጥ ኃይሎች መቃወም ማለት የወያኔን እድሜ ማራዘም ስለሆነ ከዚያ ይልቅ ተቀራርቦ በመወያየትና በመደራደር ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ነገር መስራት የተሻለው አማራጭ ነው። በሲያትሉ ጉባኤ ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉን አሳታፊ የውይይት መድረክ አዲስ አበባ ላይ ተዘጋጅቶ በሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መምከሩ የለውጥ ሂደቱን ይበልጥ የሰመረ እንደሚያደርገው እገምታለሁ።

ከላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መልካዓ-ምድር በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ ነው። ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ አንዣብቦ የከረመው የእርስ በርስ ግጭትና የሀገር መበታተን አደጋ ተወግዶ በሰላም አብሮ የመኖር የተስፋ ጭላንጭል መታየት ጀምሯል። ብዙ ወደፊት በውይይትና በድርድር የሚፈቱ ነገሮች ቢኖሩም በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ስልጣን በተቆጣጠሩ ኃይሎችና ተፎካካሪዎች መሃከል ያሉ ልዩነቶች እየጠበቡ መጥተዋል። ለዚህም ነው– እስካሁን ከምንሰማቸው እና ሲያደርጉ ከምናየው — ዶ/ር አብይን መቃወም ማለት ለአንዳንዶች ከራስ እምነትና አቋም ጋር መጋጨት ብቻ ሳይሆን በከፋፍለህ ግዛ መርህ ለሚያምነው ለወያኔ ዘረኛና አምባገነናዊ ስርዓት መቀጠል መመቻቸት የሚሆነው።

ይህ የተስፋ ጭላንጭል ሙሉ ብርሃን እንዲሆን ሁላችንም እንትጋ !

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top