Opinion & Analysis

የናፍቆት አባት #EskinderNega (Tariku Desalegn Miki)

የናፍቆት አባት

ከዳላስ አየር ማረፊያ እስከ ማርቲን ሉተር ኪንግ የዘለቀው ፈንጠዝያና የደስታ ግርግር ተግ ብሏል። የዲሲ ጀምበር ብርሃኗን ለሰው ሰራሹ ኤሌትሪክ አስረክባ መሰናበቷ የቀኑ መምሸት አዋጅ ነውና ደስታቸውን ለመግለፅ የመጡ እንግዶች አንድ አንድ እያሉ ወደ የቤታቸው እየተመለሱ ነው። ምሽቱ እየጠነከረ ሲሄድም የመጨረሻው እንግዳ ተሰናብቶ ወጣ። በሩ ተቆለፈ ።
…አሁን ቤት ውስጥ በአካል የሰማይን ያህል ተራርቀው የቆዩት፣ በመንፈስ ግን እርስ-በእርስ የተዋሀዱት ሶስት ሰዎች ብቻ ቀርተዋል። አዲስ መጪው እስክንድር ነጋ የጉዞውም የደስታውም ድካም ቢጫጫነውም ይችን ዕለት አብዝቶ ሲናፍቅ ነበርና ትከሻው ላይ ጋቢውን ጣል አድርጎ ሶፋው ላይ ተቀምጧል። ይህን ጊዜም ፊት ለፊቱ ከተቀመጠው ትንሹ ናፍቆት ጋር አይን ለአይን ተፋጠጡ፤ አባት ፈገግ አለ፤ ልጅ ለአመታት በጨቅላው አእምሮ ሲያብሰለስለው ቢቆይም መልስ ያላገኘለትን ጥያቄ ድንገት በማንሰት ለቅፅበት ያረበበውን ዝምታ ሰበረው:-
“ግን ለምን ታሰርክ?”
እስክንድር ለሰኮንዶች በፀጥታ ተዋጦ ከቆየ በኋላ አንድ ቃል ብቻ ተነፈሰ:-
“ለነፃነት!”
ምላሹ ያልተዋጠለት ብላቴና
“ለነፃነት!?”
ሲል ቃሉ እንዳለገባው በሚያሳብቅ አግራሞት ደገመው፤ አባት ለማስረዳት አቀማመጡን እያስታካከለ
“ልጄ ኢትዮጵያ አገራችን ታፍራ እና ተክብራ የኖረች ቀደምት አገር ብትሆንም፣ አምባ-ገነን በሆኑ ገዥዎች ሰብአዊ መብት የማይከበርባት፣ ዘረኝነት የሰፈነባት፣ ሙስና የተንሰራፋባት፣ መንግስታዊ ሽፍትነት የነገሰባት. . . ”
እያለ ሲያብራራ፣ ልጅ በተመስጦ ያዳምጣል። ይህንን ትዕይንት አንዲት ሴት ኮሪደሩ ላይ ቆም ብላ ውሉ ባለየ ስሜት ተውጣ እየተመለከተች ነው። ከአመታት በኃላ በቤቱ የጎደለው አባወራ ተሟልቶ፣ ልጅም ወግ ደርሶት አባቱን በስስት እያየና እየጠየቀ፣ አባትም እየመለሰ ስትመለከት አይኗ እንባ አቀረዘዘ፤ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሀዘን ግን አይደለም፤ የደስታ እንጂ።
ሴቲቷ ባሏን በግፍ ተነጥቃ የከረመች፣ ለአመታት እናትም አባትም ሆና ልጇን ያሳደገች፣ ለአመታት ወዲህ ባልን በማጣት፣ ወዲያ በስደት ስቃይ ስትቸነከር የነበረችው ብርቱዋ ሰርካለም ፋሲል ናት። ለመጀመሪያ ግዜ አባት እና ልጅን በጋራ እንዲህ ሲያወጉ ስታይ የደስታ እንባ አይኖቿን ሞላው ፣ የምትይዝ-የምትጥለውን አጣች፤ የምታወራው ከንፈሯ ላይ ይደነቃቀፋል፤ ደስ ብሏታል- መሳቅም ማልቀስም ግን አልቻለችም ፤ ብቻ አንዳች ነገር በውስጧ ይተረማመሳል። ድንገት አይኗን ወደ ባለቤቷ መለሰችና ለመጀመሪያ ግዜ “የናፍቆት አባት” ብላ ተጣራች ፤ ፈገግ አለ። ከዚህ ቀደም “እስኬ” ነበር የምትለው። በሁኔታው ሁለቱም ክትከት ብለው ሳቁ፤ በደስታ ስካር ውስጥ እንዳሉ ያስታውቃሉ። ናፎቆትም አባቱንም እናቱንም በአንድ ላይ በማግኘቱ ደስታው ወደር አጥቷል።
ዛሬ ይሄ ቤት ሙሉ ሆኗል። ዛሬ ይሄ ቤት በደስታ ተጥለቅልቊል። ዛሬ እኛም በዚህ ቤት ደስታ ፈንጥዘናል። ይህ ደስታ ለዘላለም ይቆይ። አሜን።
ታሪኩ ደሳለኝ ( ሚኪ)
ሚያዝያ 29/2010 ዓ.ም

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top