Opinion & Analysis

የጠቅላይ ሚኒስቴር ምርጫ

ከሚኪ አማራ

ኦህዴድ
——–
ኦህዴድ የኦሮሞ ወጣቶችንና ዉጪ ያለዉን የአክቲቪስቶች ግፊት ለመቋቋም ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ይፈልገዋል፡፡ የሚፈልገዉ ግን ለማን ወይንም ዶ/ር አብይን ለማድረግ ነዉ፡፡ ምናልባትም አባዱላንም ያን ያህል ላይጠላ ይችላል፡፡ ነገር ግን አባዱላ ምንም እንኳ ለኦሮሞ ህዝብ ጥሩ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም፡ በነለማ በኩል በቅርብ የተለየ ቅርጽ የያዘዉ ኦህዴድ ከድሮወቹ ወይም ከነ አባዱላ በተሻለ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ለማን ጠቅላይ ሚኒስቴር ለማድረግ ፍላጎቱ ቢኖርም ሁለት መሰናክሎች አሉት፡፡ አንደኛዉ ድርድር ከሌለና ወደ ምርጫ ከገቡ ከእነ ብአዴንና ደህዴን ጋር ዉድድር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም የህወሃት 45 ድምጽ ወሳኝነት አለዉ፡፡ ህወሃት ለማ መገርሳን በሌላ ካለቀየሩ ድምጼን ለኦህዴድ አልሰጥም በማለት ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ወደ ሌላኛዉ ድርጅት እንዲያዘነብል ያደርጋል፡፡ ሁለተኛዉ የፓርላማ አባል አለመሆኑ ነዉ፡፡ በርግጥ ይህን ህግ መጣስ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለማን ተጠቃሚ ለማድረግ ረጅም መንገድ ሲኬድ ብአዴን ዝም ይላል ወይ የሚለዉ ነዉ በተለይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ በእጁ እያለ፡፡ ከዚህም ባለፈ የኦህዴድ የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ጥያቄ ከታሪክ ጋር የተቆራኘ ነዉ፡፡ ኦህዴድ ዶ/ር ወርቅነህ ኦሮሞን ወክሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሚሆን ቦታዉን ብአዴን ወይም ደህዴን ቢወስድ ይመርጣል፡፡

ህወሃት
——-
ህወሃት ዶ/ር አብይንም ለማ መገርሳንም አይፈልግም፡፡ ለዚህ ምስቅልቅል ድርሻ አላቸዉ ብሎ ይከሳቸዋል፡፡ ከነሱ ይልቅ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ቢመረጥለት ደስ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ኦህዴድ እጩ አድርጎ ያቀርበዋል ወይ የሚለዉ አጠያያቂ ነዉ፡፡ በእርግጥ ደ/ር ወርቅነህ እጩ ሆኖ ወደፊት ከመጣ ተጠያቂዉ ህዋሀት ሳይሆን ኦህዴድ ነዉ፡፡ ምክንያቱም አሁን ኦህዴድ ባለዉ አቋም ሀወሃት ያን ያህል ተጽእኖ አድርሶና የኦህዴድን እጅ ጠምዝዞ ወርቅነህ ገበየሁን የማስመረጥ አቅም የለዉም፡፡ ህወሃት ብአዴንንም ላለማስከፋት በእጅጉ እየጣረ ነዉ፡፡ የኦህዴድን አቅም መፍጠር ባላንስ የሚያደርግለት ብአዴንን ወደራሱ በማቅረብ ነዉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛዉ ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ለማ ወይም ዶ/ር አብይ ይሆናሉ የሚል አዝማሚያ (expectation) ስላለ፡ ህወሃት ለብአዴን ደፍሮ ይሰጣል (ድምጹን) ወይ የሚለዉ አጠያያቂ ነዉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ህወሀት ብአዴንን ላለማስከፋት ሰሞኑን ይደረጋሉ ተብሎ የማይታሰቡ ነገሮችን ሁሉ እያደረገለት ነዉ፡፡ ለምሳሌ የእነ ኮሎኔል መፈታት፤ እነ አሳምነዉ ጽጌን ለመፍታት መወስን፡፡ ምናልባትም እኒህ ድርጊቶች ብአዴንን ለመደለልና የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ቦታ ጥያቄ ትቶ ምክትልነቱን ይዞ እንዲቀጥል ይሆናል፡፡ ህወሃት ከዚህ በፊት አማራን ነበር አላምንም የሚለዉ፡፡ የኦሮሞን ጥያቄም ህገምግስታዊና ተገቢ እያለ ሲያንቆለጳጵስ ነበር፡፡ ኮንተሮባንዲስት ተብሎ ከክልሉ ከተባረረ ወዲህ ኦሮሞንም አላምንም ብሏል፡፡

ብአዴን
——
ብአዴን እጅግ ሲበዛ የቅቡልነት ችግር (legitimacy crisis) ዉስጥ ገብቷል፡፡ የሚያስተዳድረዉ ህዝብ ብአዴንን ከመጤፍ አይቆጥረዉም፡፡ ህዝቡም ከትንሽ እስከ ትልቅ አማራ አይደለም ለአማራ ጥቅም የቆመ አይደለም በሚል ይተቸዋል፡፡ ይሄን ብአዴንም ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡ በፌደራል ደረጃም ይሄ ነዉ የሚባል ስልጣን የለዉም፡፡ ከዛም በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር በመሆን ለብዙ ዘመናት ሲመራ ቆይቷል፡፡ ስለዚህም አሁን ጠቅላይ ሚኒስቴር ከራሱ አባል ባያስመርጥ የሚደርስበትን ተጨማሪ ኪሳራ ያዉቃል፡፡ ለዛም ነዉ ድርድሩ የረዘመዉ፡፡ አንደኛ እጩ አቅርብ ቢባል እንኳን ማነን እንደሚያቀርብ እስካሁን አለመወሰኑ በተለይም በደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርነት አለመወሰኑ፡፡ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስቴር ባይሆን እንዴትና በምን እንደሚያስተባብል መፍትሄና ዘዴ በማፈላለግ ላይ የተጠመደ ይመስላል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አብሮ ስላልተባረረ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆን ህጉ እራሱ ይፈቅድለታል፡፡ ብአዴን ቢጠይቅም ጥያቄዉ ህገ መንግስታዊ ነዉ፡፡ አሁን እየተጠበቀ ያለዉ የብአዴን ግምገማ ዉጤት ነዉ፡፡ ምናልባትም ብአዴን ግምገማዉን እንደጨረሰ የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ጉዳይ አብሮ ያልቅ ይሆናል፡፡

ደህዴን
—-
ህወሃት ሰሞኑን ስራ በዝቶበታል፡፡ በተለይም ከኦህዴድና ከብአዴን ጋር ያለዉን ድርድር በመምራት በኩል፡፡ በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከወረደ በኋላ የደህዴንን ስብሰባ የኔ ብሎ አልያዘዉም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ደህዴን የህወሃትን ቀኝ እጅ ሽፈራዉ ሽጉጤን ገምግሞ ከደረጃ ዝቅ አድርጎ መግለጫዉን ያወጣል፡፡ ህወሀት ይሄን ሲሰማ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ደህዴንን እንዲያስተካክል ይነግረዋል፡፡ ደህዴን የፌስቡክ አካዉንቴ ሀክ ተደርጌ ነዉ በማለት እንደገና ለስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ሃይለማሪያምን ደህዴን አሰናበተዉ የሚለዉም የማይመስል ነገር ነዉ፡፡ ሲጀምር ስብሰባዉ አልቆ ሂስና ግለሂስ ተደርጎ ነዉ አመራር የሚሰናበተዉ፡፡ ደህዴን ግን ገና ስብሰባዉን እንደጀመረ ነዉ በፍጥነት ሃይለማሪያምን አነሳሁ ያለዉ፡፡ እሱን አነሳሁ ካለ በኋላ ስብሰባዉ ቀጥሏል፡፡ ስለዚህም የሃይለማሪያም መዉረድ ከደህዴን አቅም በላይ ነበር ማለት ነዉ፡፡ ደህዴን ያለ ህወሃት ሳንባ መተንፈስ አይችልም፡፡ ደህዴን እጩ ሊያቀርብ የሚችለዉ ከኦህዴድና ከብአዴን ህወሃት እንዲመረጥ ካልፈለገና እንዲሁም በኦህዴድና በብአዴን መካከል ዉድድር ካለ ነዉ፡፡ ደህዴን እጩ ለማቅረብ እንደ background ሊወስድ የሚችለዉ ሁለተኛ ተርሜን አልጨረስኩም የሚል ይሆናል፡፡

የኦሮሞ አክቲቪስቶች
——-
የኦሮሞ አክቲቪስቶች ለማን እንጅ ዶ/ር አብይን እንደማይፈልጉ አስታዉቀዋል፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆን በግልጽ አልታየኝም፡፡ ምናልባትም ሚስቱ አማራ ስለሆነች ሊሆን ይችላል( እናቱ ይላሉ ግን የተረጋገጠ ወሬ አይደለም)፡፡ ለማም ዶ/ር አብይም ያን ያህል የተለየ አቋም አላየሁባቸዉም፡፡ ሁለቱም የመደጋገፍና አብሮ የመስራት ዝንባሌ ያላቸዉ ይመስላል፡፡ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሁለቱንም ሲያደንቋቸዉ ነዉ የከረሙት፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ዶ/ር አብይን አይንህን ላፈር ብለዉታል፡፡ ይሄ የሰዉየዉን ስነ ልቦና እጅግ የሚጎዳ ይሆናል ቢመረጥም እንኳን ኮንፊደንስ ተሰምቶት ይመራል ወይ የሚለዉ አጠያያቂ ነዉ፡፡ ሲያማርጡ ግን ሁለቱንም ያለማግኘት እድላቸዉ ከፍተኛ ነዉ፡፡

ሕወሃት ለማ መገርሳን የኦሮሞ አክቲቪስቶች ዶ/ር አብይን የማይፈለጉት ምክንያት ሁለቱም ያለመተማመን ጉዳይ ነዉ (It is a matter of trust)፡፡ ህወሃት በአይጋ ፎረም በኩል ለማን አናምነዉም ብሎ ጽፏል፡፡ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ደግም ዶ/ር አብይን አናምነዉም ብለዋል፡፡

ግንቦት ሰባት
——-
ግራ የሚያጋባ ነገር ነዉ፡፡ ግንቦት ሰባት የኦህዴድ ደጋፊ ሁኖ መቷል፡፡ ዶ/ር አብይንም ይሁን ለማ መገርሳ ለኛ ሁለቱ እኩል ናቸዉ ብሏል፡፡ ከሁለት አንዱ ወደ ስልጣን ከመጡልን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል ብለዋል፡፡ አላማችን ጨለማይቱ ኢትዮጵያን በብርሃን ለመተካት ነዉ የተባለዉ ፕሮጀክት ያለፈበት ይመስላል፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያዉያን
——-
እንደ ሶማሌ፤አፋር፤ጋምቤላና ቤኒሻንጉል የሚባሉት አካባቢዎች በዚህ የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ እንደ ጎረቤት አገር ዜጎች መታየታቸዉ ትክክል አይደለም፡፡ ዛሬ አቅም ስላልፈጠሩና ጠያቂ ስሌለለ እንጅ ይሄ ከፍተኛ መድሎ ነዉ፡፡ ምናልባትም አኒህን ዜጎች ወደ ዳር የሚገፋና ወደፊትም ይሄን መገለል እንደ ታሪካዊ ምሳሌ እየተጠቆመ የህገር አንድነት ላይ ችግር የሚፈጥር ይሆናል፡፡ አሁን ያለዉ ማግለል የዛሬ 15 እና 20 አመት እንደምሳሌ እየተነሳ ልክ ዛሬ እኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር ካልሆንኩ አገር ገደል ይግባ አይነት አመለካካት መፈጠሩ አይቀሬ ነዉ፡፡ ልክ ሌላዉ ለይስሙላ እንደሚሳተፈዉ፡ቢያንስ የይስሙላ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዉ ነበር፡፡

ማስታወሻ፡፡
———
አይጋ ፎረም ላይ በተለጠፈ የአባይ ጸሃይ የትግርኛ ንግግር ተስማምተን ካልሰራን ማንም አሸናፊ ስለማይሆን ለመጠፋፋት ዝግጁ መሆናችን ሊታወቅ ይገባል፡፡ እኛም ተናግረናል እነሱም ተናግረዋል ብሏል፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ሃሳባቸዉን መያዝ አልቻልነም ብሏል፡፡ አይጋ ፎረም ገብታችሁ ስሙት፡፡ዉስጥ ላይ ያለዉን ሽኩቻ ግልጽ አድርጎ ያሳያል፡፡ ነገሩ ጡዟል፡፡

Share
error0

Facebook Comments

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

The Latest Ethiopia News

To Top