Amharic

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መቀሌ እና አዲስ አበባ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሚመሩትን ፓርቲ በገረሱ ቋንቋ «ፎርማል» እና «ኢንፎርማል» በሆነ መንገድ ተቆጣጠሩትም አልተቆጣጠሩት፣ ዐብይ የሚመሩት ለዉጥ በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ሙሉ ድጋፍ ያለዉ መሆኑን ለማረጋገጥ አብነት መጥቀስ ጉንጭ ማልፋት ነዉ-የሚሆን።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ፣የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በጋራ ከሠሩ ሐገሪቱን ከለዉጥ ማግሥት ጀምሮ የገጠሙ ግጭት፣ ቀዉሶችን ማስወገድ «ቀላል» ነዉ ይላሉ።አቶ ዳዉድን ባነጋገርን ማግሥት አዲስ አበባ ሕገ-መንግስት የፀደቀበትን ዕለት የ«በብሔር ብሔረሰቦች» በተባለዉ ድግስ ስታከብር፣ ትግራይ በሁለተኛ ሳምንት የተቃዉሞ ሰልፍ ዘከረችዉ።የትግራይ መሪ ለሰልፈኛዉ ያስተላለፉት መልዕክት ደገሞ አቶ ዳዉድ «ቀላል» ያሉት ችግር፣ ከተቃዋሚ እና ከገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ይልቅ በገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ልዩነት ሊባባስ እንደሚችል ጠቋሚ ነዉ።የተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶችን የሚያብጠዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ እንዴትነት፣የፖለቲከኞችዋ አንድነትና ልዩነት እስከየትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የገዢ ፓርቲ ይሁኑ፤ የተቃዋሚ፣ ጥቃማቸዉ የተነካ ይባሉ-ለዉጥ አራማጅ አንድ አቋም መያዛቸዉን ባንድ ነገር ያረጋግጣሉ።የሐዘን መግለጫ።ወልቃይት-ጠገዴ-ፀገዴ፣ ይሁን ሞያሌ፣ ወለጋ ይባል ጂጂጋ ፣ ጉራጌ ሆነ ጭልጋ፣ አሶሳ ይድረስ ጭናቅሰን፤ ቴፒ ይሁን ቡራዩ ሁሉም ሥፍራ ሰዎች በተገደሉ-በቆሰሉ፣ በተፈናቀሉ ቁጥር ሐዘን-ቁጭቱን የማያዥጎደጉድ ፖለቲከኛ በተለይም የገዢ ፓርቲ ባለስልጣን የለም።ሰሞኑንም ቢያንስ ሁለቱ ደገሙት።
«በምዕራብ ኦሮሚያ በተፈጠረዉ ግጭት ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ህዝቦቻችን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለዉ፣ ለትልቅ ችግር ተጋልጠዋል፣ የተጉጎዱም ሰዎች አሉ።በዚህም የተነሳ በኦሮሚያ ዉስጥ በተለያዩ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ እየተደረገ ይገኛል። ከማህበሰረቡም ዉስጥ የተለያዩ ቅሬታዎች እየተነሱ ነዉ። የተፈጠረዉ ትልቅ ችግር ማህበረሰባችንን ክፉኝ ጎድቶታል።ለተጎዳዉ ማህበረሰብም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትልቅ ሃዘን ተሰምቶታል።»
የኦሮሚያ ርዕሠ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ።ሮብ።ቅዳሜ ተረኛዉ የትግራይ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ዶክተርደብረ ፅዮን ገብረሚካኤል ነበሩ።ዶክተር ደብረ ፅዮን እንዳሉት ለጉዳተኞች ሐዘን መግለፅ የመጀመሪያቸዉ አይደለም።

«በዚሕ አጋጣሚ፣ በመላዉ የሐገራችን ክፍል በማንነታቸዉ ምክንያት በደረሰባቸዉ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸዉ የተሰማንን ሐዘን በድጋሚ እየገለፅን፣ ከጎናቸዉ ቆመን
እንደምታገል እና እንደምንደግፋቸዉ መግለፅ እንወዳለን።»

ይበሉ እንጂ አንድም ፖለቲከኛ ለተጎጂዎች የሰጠዉን ወይም ለመስጠት ያቀደዉን ካሳ እስካሁን ይፋ አላደረገም።ሌላ ቀርቶ የሟች፣ ቁስለኛ ስደተኛዉን ቁጥር እንኳ በይፋ አላስታወቁም።እርግጥ ነዉ ከተደጋጋሚ የሕዝብ ጥያቄ፣ የአደባባይ ሰልፍ እና አቤቱታ በኋላ የፌደራሉ መንግሥት እና የተወሰኑ የክልል መስተዳድሮች መፍትሔ ፍለጋ አንድ-ሁለት ማለታቸዉ አልቀረም።
የፌደራሉ መንግሥት ግጭት ወዳለባቸዉ አካባቢዎች ፀጥታ አስከባሪ አዝምቷል። ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታዉቋልም።የኦሮሚያ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ችግሩን ለማስወገድ ከተቃዋሚ የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ተስማምቷል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ እንደሚሉት ሥምምነቱ ከኦሮሚያ አልፎ በመላዉ ኢትዮጵያ ፀጥታ ለማስፋን የሚረዳ ነዉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ እና ተንታኝ አቶ አበባዉ አያሌዉ እንደሚሉት ግን ግጭት ሁከቱን ለማስቆም የአጭር ጊዜዉ መፍትሔ ሥልጣን ላይ ባሉት ሰዎች እጅ ነዉ።አቶ አያሌዉ እንደሚሉት ግጭቱን እና ግጭት ቆስቋሾችን ለመቆጣጠር የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናት ሰወስት ነገሮችን ማድረግ አለባቸዉ።
ግጭት ሁከቱ ጎሳን ወይም ብሔርን ሰበብ ያደረገ መሆኑን የካደ ባለስልጣን፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ፤ የፖለቲካ ተንታኝ እና ታዛቢ የለም።ይሁንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለግጭት ግድያ መሠረታዊ ምክንያት እንኳን ባይሆን ሰበብ ለሆነዉ ለጎሳ አስተዳደር ሕጋዊ ዋስትና የሰጠዉ ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት ዕለትን ወይም «የብሔር ብሔረሰቦች ቀን» ለአስራ-ሰወስተኛ ጊዜ አስከበሩ።ቅዳሜ።
አዲስ አበባ ለኢሕአዲግ የሥልጣን መሠረት የሆነዉ ሕግ የፀናበትን ዕለት ለማክበር በጭፈራ፤ ፌስታ፣ደስታ ስትቦርቅ የኢሕአዴግ መስራች፣ ምናልባትም የጎሳ ፖለቲካ ዋና አቀንቃኙ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) ያደራጀዉ ሰልፈኛ መቀሌን አጥለቅልቋት ዋለ።
የሠልፉ ዋና መልዕክት በተለይም የሕወሐት ሊቀመንበር እና የትግራይ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር የዶከተር ደብረ ፅዮን ንግግር የኢሕአዴግ መሪዎች ሠላም ለማስፈን በጋራ መቆማቸዉን በርግጥ አጠያያቂ አድርጎታል።

ሠልፉ እና መልዕክቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አሕመድ ገዢዉን ፓርቲ ኢሕአዴግን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ችለዋል ወይ የሚል ጥያቄ ያጭራልም።የፖለቲካ አቀንቃኝ እና ተንታኝ ገረሱ ቱፋ አይ-አዎ ዓይነት ነዉ መልሳቸዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሚመሩትን ፓርቲ በገረሱ ቋንቋ «ፎርማል» እና «ኢንፎርማል» በሆነ መንገድ ተቆጣጠሩትም አልተቆጣጠሩት፣ ዐብይ የሚመሩት ለዉጥ በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ሙሉ ድጋፍ ያለዉ መሆኑን ለማረጋገጥ አብነት መጥቀስ ጉንጭ ማልፋት ነዉ-የሚሆን።የዚያኑ ያሕል ሥልጣን እና ጥቅማቸዉን ያጡ ኃይላት በተለይ የሕወሐት ሹማምንት ለዉጡን ለማጨናጎል ግጭት-ሁከት ማቀጣጠልን እንደ ጥሩ ሥልት እየተከተሉት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።የታሪክ ምሁር አበባዉ አያሌዉ አንዱ ናቸዉ።

አንጋፋዉ ፖለቲከኛ ዳዉድ ኢብሳ ሥለ ሕወሐት እና አባላቱ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ የሰጡት መልስ ከአንጋፋ ፖለቲከኛነት ይልቅ የአንጋፋ ዲፕሎማት ዓይነት ነዉ።የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያብጠዉን ግጭት በቀድሞዉ ሥርዓት ሐብት ያካበቱ እና በስለላዉ መዋቅር ዉስጥ የነበሩ ኃይላት እንደሚያቀጣጥሉት «መሬት» ላይ ይታያል ይላሉ-አቶ ዳዉድ ።
ይሁንና ሕወሐት በተደረጀ መልኩ ወይም መሪዎቹ እና አባላቱ በተነጣጠለ ሁኔታ በግጭት ሁከቱ መሳተፍ አለመሳተፋቸዉን የሚያረጋግጥ መረጃ ሊኖረዉ የሚችለዉ መንግሥት ነዉ።

ለመቆጣጠር አብነቱ አቶ ዳዉድ እንዳሉት በጋራ መቆም ነዉ።በጋራ እንቁም የማይል ፖለቲከኛም በርግጥ የለም።እስካሁን ግን 80 እና 70 ሆነዉ መለያየታቸዉን እንጂ በጋራ መቆማቸዉን ያስመሰከሩ ፖለቲከኞች አለመኖራቸዉ ነዉ-አስተዛዛቢዉ ሐቅ።አቶ ዳዉድ ኢብሳ ግን መተባበሩ ብዙ አያቅትም ባይ ናቸዉ።ግጭት-ሁከቱም ለኢትዮጵያ ብዙ አያሰጋም።

ሌሎች ብዙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች ግን ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ናት ይላሉ።አንድም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ታመራለች።አለያም ትበታተናለች።ጥያቄዉ «ማን በየትኛዉ ጎዳና ያስኬዳት ይሆን?» ነዉ።

Via DW Amharic

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top