Ethiopia News

ይድረስ ለሃይሌ ገ/ስላሴ – ከሰይፈ ቴክሳስ ኦስተን

ሃይሌ ገ/ስላሴ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኋይለስላሴና ከአበበ በቂላ በመከተል ወይም በሚመጥን በሚባል መልኩ ኢትዮጵያ በበጎ መልኩ የምትታይበት ነገር ባጣችበት ዘመን፣ በበጎ እንድትታይ በማድረግህ እንዲሁም የተረሳችው ኢትዮጵያ ባንዲራዋ በአለም አደባባዮች ከፍ ብላ እንድትታይ ምክንያት በመሆንህ ከኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ማግኘትህ አሌ የማይባል ሃቅ ነው፡፡ ለአላማህ በአለህ ጽናት ለሌሎች ምሳሌ መሆን በመቻልህ፣ ከአንተ በኋላ የመጡ አትሌቶች የአንተን ፈለግ በመከል ትጋትና ጽናት ኖሯቸው ለውጤት እንዲበቁ ማድረግህ ደግሞ ወደ ውስጥ ገባ በማለት ስለአንተ ስንመረምር ልናገኝ ከምንችላቸው ከብዙ በጥቂት የሚጠቀስ እውነታ ነው፡፡

እነኝህ መልካም ነገሮች እንዳሉህ ብንረዳና ስለ አንተ የታዘብናቸው ክፉ ነገሮች ቢኖሩም፣ ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው እሳት ሆነባት፣ እንዳትተወው ልጇ ሆነባት የሚባለው ነገር ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ የሆዱን በሆዱ እየያዘ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ሲል ቢከርምም ሃይሌ ግን ያንን ዝምታ ከጅልነት ቆጥረኸው ይሁን፣ ሀብትና ዝና መሸከም ከምትችለው በላይ ሆኖብህ በግልጽ ባልረዳውም የህዝብን ስሜት የሚጎዱ ነገሮችን እየደራረብክ ከህዝብ ጋር ያለህን ግንኙነት ንፋስ እያስገባህበት መሆኑን ያስተዋልከው አትመስልም፡፡ በተለያዩ የመገናኛና የማህበራዊ ሚዲያዎች ከምርጫ 97 የቅንጅት መሪዎች ሽምግልና ጀምሮ አሁን ላይ እስከገለጽከው ከገዳዮች በደል በላይ የተበዳዮች እምቢተኝነትን እንደጥፋት አድርገህ እስከ ማቅረብ የሄድክበት መንገድ ዋጋ ሊያስከፍልህ እንደሚችል ማሰብ የሚገባህ ይመስለኛል፡፡

እውነት ነው፡፡ አገር ቤት ሆነህ ብዙ ሃብትና ንብረት አፍርተህ የምታይ የምትሰማውን እውነታ መግለጽ ዛሬ ላይ ብዙዎችን ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል እያየህ ግባበት ብሎ መመከር አይቻልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው የመንፈስ ልእልና እጅግ በጣም የሚለያይ እንደመሆኑ መጠን፣ የአቅምህን  እንጂ ከአቅምህ በላይ መሄድም እንደማትችል እገነዘባለሁ፡፡ ሆኖም ግን የህይወት ስሌትህ በትርፍና ኪሳራ የተመሰረት ከሆነ እንኳን፣ በዛሬው ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሌት መስራትህ ነገህን እንድታጣው ያደርግሃል፡፡ ነገ ይህ እየተንቦገቦገ እየመጣ ያለው ወጣት ትውልድ ነው፡፡ የዛሬ ባለ ቀኖች ዛሬን የሚኖሩት አሟሟታቸውን እያሰበቡ፣ የቀብራቸው ቦታ እየመረጡ የቁም ተስካራቸውን እየበሉ የሚገኙ ሙታን ናቸው፡፡ የነገዎቹ ባለቤቶች ግን ስለሞት፣ስለቀብር ደንታ የሌላቸውና ነጻነቴን የሚሉ ሞትን የማይፈሩ አፍላ እድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚንገታገቱት የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ አዛውንቶች፣ በፈጣን ሁኔታ ስልቱን እየቀያየረ  የሚመጣውን ፈጣን አስተሳሰብ በሚኖርበት እድሜ ላይ ያለውን ወጣት ተቋቁመው ነገን በተአምር አይሻገሯትም፡፡ ይሄ ትንቢት አይደለም የተፈጥሮ ኡደት የሚያሳየን ሃቅ ነው፡፡

ሃይሌ ከአንተም በበለጠ ከልጅ እስከ አዛውንቱ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለው የትዝታው ንጉስ መሃሙድ አህመድ፣ የትግራይ ነጻ አውጪዎቹ ስልጣን እንደያዙ እሼሼ ገዳሜ ማለት ሲያበዛ የኢትዮጵያ ህዝብ ወዲያውኑ አንቅሮ ነው የተፋው፡፡ እርስ በእርስ በመተባበር የሚታወቀው የጉራጌ ብሄረሰብ እንደዛሬው ሳይሆን በንግዱ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን የያዙ እንደመሆናቸው፣ እነሱ ብቻ ከሀብት ማማ ላይ ሊያወጡት ሲችሉ በአገር ጉዳይ ቀልድ የለም ብለው ከህዝብ ጋር ተባብረ  ከጨዋታ ውጪ  ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውሳታና ከመሃሙድ ከእራሱም ልትሰማው የምትችለው ሌላው ሃቅ ነው፡፡ በህዝብ ልብ ውስጥ ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ መሃሙድ ብዙ መከራ አይቷል፡፡ እኔ በግሌ እንኩን ድሮ ዘፈኑን ብቻ ሳይሆን መሃሙድን ጨምሬ በጣም እወደው  እንዳልነበር፣ዛሬም ድረስ የሻከረው ልቤ ለዘፈኖቹ እንጂ ለመሃሙድ የድሮው ቦታው ላይ መመለስ አቅቶታል፡፡ ስንት የእኔ ብጤዎች ይኖሩ ይሆን?

ስለዚህ አንተም በጊዜ መማር ካልቻልክ የአንተው በጣም የከፋ መሆኑን  አትጠራጠር፡፡ አሁን ብዙ ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ ደም በፈሰሰ ቁጥር ምሬት እየጨጨመረ ሄዶ ከትእግስታና ፍርሃት ወጥቶ ያለ ነጻነት አልኖርም በሚል በመንግስት መገደል ብቻ ሳይሆን ለመሞት የተቆረጠበት ዘመን መሆኑን ልታስተውል ይገባል፡፡ ሞትን የሚያስመርጠው የእስር ቤት ስቃዮችን ተቋቁመው በምህረት የወጡት የመብት ተሟጋቾች ዛሬም ለወጣቱ ያስተላለፉት መልእክት፣ ግባችሁ እኛን ማስፈታት ሳይሆን የታሰርንለትን አላማ ማስፈታት መሆን አለበት፡፡ እኛም ትግላችንን ቀጥለን ያንን ስቃይ በድጋሚ ቢመጣም እንቀበለዋለን በማለት እየጮኹ እንደሚገኙ ልብ በል፡፡ ዛሬ ድቅድቁን ጨለማ ለመሻገር ጥቂት ሰአታት ቀርቶናል፡፡ እንደነ አርቲስትና አትሌት እገሌ አርበኛ መሆን  ቢያቅትህ ያለህን የህዝብ ፍቅር ይዘህ በድል አጥቢያ አርበኝነት እንኳን ለመቀላቀል እራስህን አዘጋጅ፡፡ እምቢ ካልክና እንደ ጨው መጣፈጥ ካልቻልክ የሚጠብቅህን ጊዜው ሲደርስ ታየዋለህ፡፡ ዛሬም ህዝብ ይወድሃል፡፡ ግንኙነትህ ሳስቷል እንጂ አልተበጠሰምና  አስብበት። አድናቂህ

Share
error0

Facebook Comments

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

The Latest Ethiopia News

To Top