Amharic

ኦዴፓና ኦነግ ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ተጠየቀ

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን ለማስቆም የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ /ኦዴፓ /እና በቅርቡ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት የገባዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ችግራቸዉን በዉይይት ሊፈቱ ይገባል ሲል የኦሮሞ ብሄራዊ ጎንግረንስ /ኦብኮ/ አሳሰበ።

ፓርቲዉ በዛሬዉ ዕለት በሰጠዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ በኦነግ እና በኦዴፖ መካከል የተደረገው ስምምነት ግልጽ ባለመሆኑ ስምምነቱን ይፋ በማድረግ ሁለቱ አካላት ለመፍትሄ እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የብዙ ሰዎችን ህይወት ያጠፉ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል።ከሰሞኑም በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ግጭቱ ቀጥሎ 8 ሰዎች መገደላቸዉ እየተነገረ ነዉ።መንግስትም እነዚህን ግጭቶች ለዉጡ ያልተዋጠላቸዉ አካላት የቀሰቀሱት ነዉ በሚል በደፈናዉ ሲገልፅ ቆይቷል።

ካለፈዉ ሳምንት ወዲህ ግን ፤ ግጭቶቹ በሀገሪቱ የመጣዉን ለዉጥ ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር የገባዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር / ኦነግ / እና የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ /ኦዴፓ/ አንዱ በአንዱ ላይ ጣት መቀሳሰር ይዘዋል።ጉዳዩ አሳስቦኛል በሚልም የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረንስ በዛሬዉ ዕለት መግለጫ አዉጥቷል።የፓርቲዉ ሊቀመንበር አቶ ቶለሳ ተስፋዬ ለDW እንደገለፁት ኦዴፓና ኦነግ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በሰከነ መንገድ ችግራቸዉን ሊፈቱ ይገባል።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ በሁለቱ ሀይሎች መካከል የሚካሄደዉ ግጭት የህዝቡን ህይወት ንብረትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ጥሏል።

ኦነግና ኦዴፓ በየፊናቸዉ ከሚሰጡት መግለጫ በመነሳት በመካከላቸዉ ጥርጣሬ መኖሩን አቶ ቶለሳ ጠቁሙዉ ይሁንና ፓርቲዎቹ ለህዝቡ ችግር ቅድሚያ በመስጠት መደማመጥ አለባቸዉ ነዉ ያሉት።በጋራ የተስማሙበትን ጉዳይም ፓርቲዎቹ ለህዝቡ ይፋ ማድረግ እንዳለባቸዉም አመልክተዋል።

«ችግሮች ደግሞ ለህዝብ በይፋ በግልፅ መነገር አለባቸዉ።አሁን ህዝብ የሚያዉቀዉ ነገር የለም።በአደባባይ ወጥተዉ ሁለቱ ፓርቲዎች የተስማማንበት ይህ አንቀፅና ይህ ነጥብ ነዉ ።እከሌ ይህን አፈረሰ የሚል ነገር የለም ።እከሌ አፈረሰ፤እከሌ አፈረሰ በደፈናዉ ነዉ።ህዝቡ መረጃ የማግኜት መብት አለዉና ስለዚህ ትክክለኛዉ ነገር ትክክለኛዉን መረጃ ለህዝቡ መስጠት አለባቸዉ።»

ህብረተሰቡም የፓርቲዎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ከመሆን ወጥቶ በዕጁ ያለዉን ሰላም እንዲያስጠብቅ አሳስበዋል።
«ህብረተሰቡም ደግሞ መምከር አለባቸዉ።የሀገር ሽማግሌዎችም፣አባ ገዳዎችም ወደ በረሃ እየገባ ያለዉን ወጣት መከልከል አለባቸዉ።መገሰፅ አለባቸዉ ።»ካሉ በኋላ «ህዝቡ ሁለቱንም/ፓርቲዎች/ መዳኜት አለበት።ዋናዉ ህዝብ ነዉ።ህዝቡ ካልተባበረ ፣መንገድ ካልዘጋ፣ወጣቱ ካላበረ፣ ሁለቱም ከዉሃ እንደወጣ ዓሳ ነዉ የሚሆኑትና ህዝቡ በፍፁም ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት።» ብለዋል።

መንግስት በበኩሉ የዜጎችን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ሃላፊነት ያለበት ቢሆንም ፤በአካባቢዉ ጦር ከማሰማራቱ በፊት በሆደ ሰፊነት ለሰላማዊ መፍትሄና ለዉይይት ቅድሚያ ይስጥ ሲሉ ምክር ለግሰዋል። ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ቢሮ ሀላፊዎችንና የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ባለስልጣናትን ለማነጋጋር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።

Via DW Amharic Original Article

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top