Amharic

“ሃገሬን ሳላስብ የዋልኩበት፤ ያደርኩበት ቀን የለም” ብርቱካን ሚደቅሳ | Birtukan Mideksa

(BBC Amharic) ዛሬ ማለዳ ከሰባት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የገቡት የቀድሞዋ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከተለመደው የአቀባበል አጀብ ይልቅ በጥቂት ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው ብቻ የተወሰነ እንዲሆን መርጠዋል።

ብርቱካን ሚደቅሳ (Birtukan Mideksa)

በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በሚገኘው የቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ሲደርሱ ግን የአካባቢው ማህበረሰብ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎላቸዋል።

በግቢው የእርሳቸውን ጽናትና ብርታት የሚዘክሩ የተለያዩ መልዕክቶች ከምስላቸው ጋር የተሰቀሉ ሲሆን ወጣቶችም በከነቴራቸው ፎቶግራፋቸውን አትመው ድጋፍና ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል።

managed wordpress hosting

“ባለፉት ሰባት ስምንት አመታት ያለፈው ቀላል ነገር አይደለም፤ በእያንዳንዱ ቀን እናንተን ሳላስብ፤ የሃገሬን ሰው ሳላስብ፤ ሃገሬን ሳላስብ ያደርኩበት፣ የዋልኩበት ቀን የለም።

ብዙ ቀን የማንተያይ፣ የማንገናኝ መስሎኝ ያውቃል፤ ግን ይኽው ዛሬ ተገናኘን” ብለዋል ወይዘሪት ብርትኳን ስሜታቸውን በሲቃ በገለጹበት አጭር መልዕክታቸው።

“ብዙ ችግር አሳልፈናል፤ ይሄኛው ግን ይለያል። ምክንያቱም ተስፋ እናያለን ፤ ካለፍነው ከዚህ በኋላ የሚመጣው የተሻለ ጊዜ ነው የሚሆነው። በሕይወታችን ብዙ ችግር አልፏል፤ የችግሩ ብዛት ሳይሆን ከችግሩ ስንወጣ ያለው ደስታ ብዛት ይበልጣል።”

ወይዘሪት ብርቱካን በንግግራቸው ህዝቡ እርስ በእርስ የመደጋጋፍና የሌላውን ጥቃት የራስ አድርጎ የመቀበል ልምዱን እንዳይተዉም አደራ ብለዋል።

“የእኔ ሃብት እናንተ ናችሁ፤ እናቶቻችን አባቶቻችን ያስተማሩን ነገርም ይኽው ነው። እንዳችን ለሌላችን ማሰብን፤ የሌላውን ሰው ጥቃት ጥቃቴ ፤ ችግሩ ችግሬ ነው ብለን ተጋግዘን ነው ያደግነው፤ እዚህም ያደረስን እርሱ ነው።”

የቀድሞዋ ቤተልሔም ያሁኗ ብርቱ-ካህን ሚደቅሳ

የብርቱካን እናት የ78 ዓመቷ አረጋዊት ወይዘሮ አልማዝ ገብረእግዚበሔር ከብቸኛ ሴት ልጃቸው ጋር ዓይን ለዓይን ከተያዩ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ሁልጊዜም እስከመቼ እንዲህ ሆነን እንዘልቃለን? እያሉ በሃዘንና በጭንቀት ይሰቃዩ እንደነበረ ነው ለቢቢሲ የገለጹት።

“ማሰቤማ የት ይቀራል? ቢጨንቀኝ እኔ ሁለት ጊዜ ሄጄ አይቻት መጣሁ፤ አሁን ልምጣና ልይሽ ስትለኝ ሳልሞት ልጄን ላያት ነው ብዬ በጣም ተደሰትኩኝ። እግዚአበሔርም ከተፍ አደረጋት ተመስገን፤ አውሮፕላን ማረፊያ ከፊት ጉብ አድርገውኝ ስጠብቃት ከተፍ አለች።”

ወንድሟ አቶ አየለ ገብረእግዚበሔር እንደሚሉት የወይዘሪት ብርቱካን የወደፊት እጣ ፈንታ ከዓመታት በፊት በአባታቸው ህልም የተፈታ ነበር።

“መጀመሪያ ሌላ ስም ነበር ያወጣንላት፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ቤተልሔም ነበር የምትባለው፤ አባቷ ግን ‘ህልም አይቻለሁ ስሟ መቀየር አለበት’ ብሎ ብርቱካን አላት። በእርግጥም አሁን እየቆየ ሲሄድ ብርቱካን በሚለው ውስጥ ቅኔ አለ፣ ብርቱ-ካህን ማለት ነው። በጣም ጠንካራ ጎበዝ ታታሪ ካህን ማለት ነው። አሁንም ከነጥንካሬዋ ከምትወደው ህዝብ ጋር እየኖረች ብትሰራ በጣም ነው ደስ የሚለን” ብለዋል።

የቀድሞዋ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ኣመራርና የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መስራችና መሪ የነበሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጥሪ በመቀበል የለውጡ አካል ለመሆን በወደሃገር ቤት ለመመለስ እንደወሰኑ ቢናገሩም በየትኛው የሥራ ቦታ እናያቸዋልን? ለሚለው የብዙሃን ጥያቄ ግን በማህበራዊ ሚዲያ ከሚንሸራሸሩት ሃሳቦች የዘለለ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

Share
error0

Facebook Comments

The Latest Ethiopia News

To Top